የካፈቾ፣ የናይ እና ጻራ ብሔር/ብሔረሰብ ቋንቋዎችን ለማሳደግ የባለድርሻ አካላት ሚና እንዲጠናከር ተጠየቀ

Spread the love

የካፈቾ ብሔር የዘመን መለወጫ (ማሽቃሬ ባሮ) በማስመልከት በተዘጋጀው የካፈቾ፣ ናይ እና የጻራ ብሔር/ብሔረሰቦች የባህልና ቋንቋ ሲምፖዚየም ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡ ምሁራን በካፋ ውስጥ ያሉ የብሔር/ብሔረሰቦችን ቋንቋ ለማሳደግ የባለድርሻ አካላት ትብብር መጠናከር እንዳለበት ጠቁመዋል።

የካፈቾ ብሔር ዘመን መለወጫ መከበር ለብሔሩ ባህልና ቋንቋ ዕድገት የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን የጠቆሙት የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ በዚህም ካፊ ኖኖ ከ1987 ዓ/ም ጀምሮ የትምህርት ቋንቋ በመሆን አሁን ላይ እስከ መጀመሪያ ድግሪ እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

ካፊ ኖኖ ከ2002 ዓ/ም ጀምሮ በዞኑ የስራ ቋንቋ በመሆን አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝም ዋና አስተዳዳሪው የገለጹት።

በተለያየ መልኩ ለብሔሩ ቋንቋ ዕድገት የበኩላቸውን ሚና የተወጡ አካላትን ያመሰገኑት ዋና አስተዳዳሪው፤ አሁን ላይ ቋንቋውን በማሳደግ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ጥናታዊ ጽሁፍ አቅራቢዎቹ በበኩላቸው የብሔሩ የቋንቋ ዕድገትን የደረሰበትን በንጽጽር ያሳዩት ሲሆን በዚህም ባለፉት 30 ዓመታት የመጀመሪያው የቋንቋ ሲምፖዚዬም ከተካሄደበት ወዲህ ትርጉም ባለው መልክ ዕድገት እያሳየ መመጣቱን አስረድተዋል።

በተፈለገው ልክ ቋንቋውን ለማሳደግ ተናጋሪዎች በመደበኛና በዕለተ ተለዕት ተግባራት ላይ ቋንቋውን መጠቀም እንደሚገባም ምክረ ሀሳብ አቅርበዋል።

በሚዲያ ቋንቋውን የመጠቀም አዝማሚያ አበረታች መሆኑን ያስገነዘቡት ጥናት አቅራቢዎቹ፡ ወጣቶች በማህበራዊ ሚዲያ አማራጭ ቋንቋውን እንደወረደ በመጠቀም ለቋንቋው ዕድገት የበኩላቸውን ሚና መጫወት እንዳለባቸውም ተጠይቋል።